ኢንተርኔት ላይ ድመት መሆንህን ማንም አያውቅም
የኮምፒውተር አሰራር ያስደምመኛል፤ ግን ጊዜ ሰጥቼው አልመረመርኩትም፥ ምንስ ሲያረግልኝ። ዘውትር ኢንተርኔት ካፌ ገብቼ ኮምፒውተሩ ፊት እንደተቀመጥኩ ቅድሚያ መጠቆሚያዉን ወደ ኢንተርኔት ማሰሻ ነው የማደርገው።
የመጀመሪያ ስራዬ ታዲያ ጉግል ከፍቼ የራሴን ስም ጽፌ ማሰስ ነው። የኔ ስም፥ አባት አልያም አያት ላይ ካልሆነ በዚህ ዘመን አይገኝም። ወዳጄ እንዳለው ከሰባዎቹ ወዲህ በኔ ስም የሚጠራ ሰው አንድ እኔ ብቻ ነኝ። እኔ ደሞ ለጉግል ጉልጎላ የሚያበቃ ምንም አበርክቶት ስለሌለኝ ከፌስቡክ ገጼ በስተቀር (እሱን ሲያመጣልኝ ታዲያ ፈ.ገ.ግ…እልና ወደኋላ ተለጥቼ ካፌው ዉስጥ ያለዉን ሰው ገልመጥ አረገዋለሁ) ጠብ የሚል መረጃ የለም፤ ጭራሽ የገዛ ስሜን አላውቀው ይመስል “እንደዚህ ማለት ፈልገህ ነው?” ብሎ ይጠይቀኛል። እሱን ተከትዬ እነጉዳለሁ፤ የመጀመሪያ መዳረሻ….ዊኪፔዲያ! እዚያ ሰምጬ እቆይና ግራ የሚያጋባኝ ነገር ሲያጋጥመኝ ስለሱ ተመልሼ ማሰስ እጀምራለሁ…። ሲነሽጠኝም ወደአማርኛው ክፍል ገባና አንዳንድ ነገሮችን ከትባለሁ። ይሄ አዙሪት ለረጂም ሰአት ይቀጥላል፤ መነሻዬ ጨርሶ እስኪረሳኝ።
እቀጥልና ፌስቡክ እገባለሁ፤ ለጓደኝነቱ ሳይሆን ግን ለወሬ ስል። ሰው ስለምን እያወራ እንደሆነ፣ ትኩስ ዜና ካለ….ብዬ ነው። መጀመሪያ ሰሞን በወረት “ጓደኛ” መጨመር፣ ቻት ማረግ፣ አስቂኝ ስዕሎችን ማየትና ለ”ጓደኞቼ” መላክ፣ ሰዉየው አክብሮት የማያውቀዉን ‘መልካም ልደት’ ማለት ወዘተርፈ…የተለመዱ የዘወትር ስራዋቼ ነበሩ።
ወረቱም አለፈና፣ የ”ጓደኞቼ” ብዛትም አሰልቺ እየሆነብኝ መጥቶ ለመቀነስ ከወሰንኩ ቆይቻለሁ። ማንን ቀንሼ ማን ይቀራል የሚለው ግን ሰፊ ጥናት የሚያሻው ተግባር ስለሆነ የጥናቱን ወጪ የሚሸፍንልኝ ተቋም በማፈላለግ ላይ እገኛለሁ። ቅነሳዉን በሦስት ዙር ለማድረግ ነው ያቀድኩት፤
፩-ኤድያ ጥቅስ ብቻ!
በአንድ ቀን ከአምስት በላይ ጥቅስ (የሼክስፒርም ይሁን የመጽሐፍ ቅዱስ) የሚለጥፉ። እነዚህ ገጼን የድሃ ቤት ግድግዳ እያስመሰሉ ያስቸገሩኝ ናቸው። የጨዋታ (ጌም)፣ የአብዮት፣..ተደጋጋሚ ጥሪ የሚልኩልኝም ከነዚህ ጋር ተደምረው በመጀመሪያው ዙር የሚሸኙ ናቸው።
፪-ዝምታም መብት ነው!
ቻት ጀምረው ከ “ሃይ” መሻገር የተሳናቸው በሙሉ በዚህ ዉስጥ ይመደባሉ። የሰው ልጅ ማውራት ካልቻለ ወይም የሚያወራው ነገር ከሌለው ዝም የማለት መብቱ በተፈጥሮ የተከበረ ነው። የመናገር እንጂ ዝም የማለት መብት በየትም ዓለም ሆነ ዘመን ተከልክሎ አያውቅም። ይህን መገንዘብ ተስኗቸዉም ይሁን በሌላም ምክኒያት ሁሌ ባዩኝ ቁጥር ቻት ማድረግ ጀምረው ሰላምታ ሰጥተው በቀጥታ ወደ “በተረፈ?” የሚገቡትን ጠቅለል ያለ ቅድመ ማስጥንቀቂያ አንዴ እሰጥና አሰናብታቸዋለሁ።
፫-ማን ልበል?
ከላይ ባካሄድኩት የማጣራት ሂደት የ”ጓድኞቼ” ቁጥር ለአስተዳደር ምቹ ወደሆነ ደረጃ ካልወረደ ወደ፫ኛ ዙር የማጣራት ሂደት ለመግባት እገደዳለሁ። የዚህኛው ዙር የማጥራት ሂደት ዒላማ የሚሆኑት ለዜና ምንጭነት የማይሆኑ፣ ወንዝ የሚያሻግር ወዳጅነት ጥንካሬ የሌላቸው እና ከጓደኝነት ይልቅ ዝምታቸው የሰላይ የሚመስልባቸው ይሆናሉ። ሆ! አንዳንዴ ፎቶ እንኳን ቀይሩ እንጂ።
በርግጥ ይሄ እጅግ የተንዛዛ አሰራር ነው ብሎ የሚተች አይጠፋም። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች በቅርቡ ከጓደኝነት በመቀነሳቸው ቀናሹን ስለገደሉት የተነገረውን ዜና ያልሰሙ መሆናቸዉን ማወቅ ይቻላል። ከተቻለ እንደዉም የሥነ ልቦና ባለሙያ ማማከር ሊናቅ የማይገባው ብልህነት ይመስለኛል። በመቀነሳቸው በራሳቸውም ላይ ሆነ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ “ጓደኞቼን” ከቅነሳው በፊትም ሆነ ከቅነሳው በኋላ ተገቢ የስነ ልቦና ምክር የሚያገኙበትን ዘዴ ከዲኬቲ ጋርም ቢሆን በመተባበር ማዘጋጀት ተገቢ ነው።…
ይህ ሁሉ ካልተሳካም ይህን ዘግቼ በሌላ ስም ሌላ ማንነት ይዤ አዳዲስ “ጓደኞች” ማሰባሰብ እጀምራለሁ። ደሞ ለፌስቡክ “ጓደኛ”….
ታዲያ ፌስቡክ ላይ ወሬ አይጠፋም። ስለ ፖለቲካ መሪዎቻችንም ይሁን ስለ ኤሚ ዋይንሃውስ ዜና ዕረፍት፣ ስለ አረፋም ይሁን ሰ ቅዱስ ሚካኤል ንግስ፣ አልያም ስለ አንዲት አስቂኝ የላስቬጋስ ድመት…። ስለሚደግፈው ሰባኪ፣ ዋንጫ ስላጣው የኳስ ቡድን፣ …ውይ ውይ ውይ ደሞ ስለተቃውሞ ሰልፍ…ኤዲያ
ይሄኔ የኑረዲንን ግጥም አሻሽዬ በዉስጤ እለዋለሁ፡
ሰልፍና መፈክር ነዳጅ ቢሆን ናፍጣ፣
መሰለፊያ ቦታ ዘወትር እንዳናጣ፤
ሲሆን በግል በግል ከታጣ በማህበር፣
ዳያስፖራ መንገድ ያሰራልን ነበር።
ሰልቸት ሲለኝ የዛችን ልጅ ፎቶ አፈላልጌ ማገላበጥ እጀምራለሁ። የታባቱ! ቤቷ ድረስ ሄጄ ያጣሁትን አልበም እዚህ በግላጭ አገኘዋለሁ። ምስጋናዬን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለፅ የማርክ ገፅ ላይ ሂጄ የአብርሃም የሳራ ይሁን ትዳራችሁ አልኩት (እሱም እዚሁ ይሆን የጠበሳት ሚስቱን ብዬ እያሰብኩ)። ታዲያ የሚገርመኝ ሁሉም ፎቶዎቿ ላይ በቄንጥ ወይ ቆማ ወይ ተቀምጣ፤ ስስም ይሁን ብርቱ ፈገግታ ከፊቷ አይጠፋም። “ሳያት የምታስቀኝ ሚስት አገባሁ” ያሉት አበው ለእሷ ሳይሆን ይቀራል?
ጠቅልዬ ከመውጣቴ በፊት ታዲያ የቀልድና ያጫጭር መልክት ጽሁፎች ያሉበትን ገጸ ድር እከፍትና በኋላ በስልክ ጓደኞቼ ላይ ጉራ ምነፋበት ቀልድና ሰሚራን የማማልልበት የፍቅር ዉዳሴዎች ጻፍ ጻፍ አርጌ ማኪያቶ ልጠጣ ወጣለሁ። ያው ከካፌ ወደካፌ ነው ነገሩ…