የዛ ትውልድ ሥንኞች
ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ
እንደ ሆ ቺ ሚኒ እንደ ቼ ጉቬራ
* * *
ሃይ ዘራፍ እያሉ እያረረ አንጀቴ
እኔስ አልረባሺም ወልደሽ ተኪ እናቴ
* * *
ውስኪውም ይንቆርቆር ጮማውም ይቆረጥ
እማዬ እኔና አንቺ ሽሮ እናሯሩጥ
* * *
ዮሜሳን ለሆዴ ማን ይገዛልኛል
እንቆቆ እየጋቱ ዶሮ ማታ ይሉኛል
* * *
እኔ ልኮራመት እኔ ከሰል ልምሰል
ስቀሽ አታስቂኝ የደላሽ ይመስል
* * *
የእምዬ ልጅ ሙቺ ዉሃ ጉድጓድ ገብተሽ
ላንቺ ሳጥን ገዝቶ ማንም ሰው አይቀብርሽ
* * *
በስምንተኛው ሺ ሲመሽ ተወልጄ
ጅቡን ጋሼ እላለሁ ተኩላውን ወዳጄ
* * *
ባንዲት ሉክ ጀምሬ አቤቱታ
ስንት ዓመት ልኑር ስንገላታ
በሸንጎ ስወጣ ስወርድ
አለቀ ስንቄ በመንገድ
አንተ የበታች ሹም መዝገብ ቤት ያለኸው
ዶሴዬን ወደታች አርገህ የቀበርከው
እንዲታይ ነው እንጂ ወደበላይ ቀርቦ
እንዲኖር አይደለም መዝገብ ቤት አጣቦ
* * *
ይሄዳል ወታደር ይሄዳል ወታደር ይሄዳል ተራምዶ
እየወረደበት ቦንብ እንደበረዶ
* * *
ወዘት በይ ልቤ እንደጀበና
አልወጣልሽም የጦር ባፈና
* * *
የፍየል ወጠጤ ትከሻው ያበጠ ልቡ ያበጠበት
እንዋጋ ብሎ ለነብር ላከበት
የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች
ልጆቿም ያልቃሉ እሷም ትሞታለች
* * *
ሃቻምናም እሮሮ ዘንድሮም እሮሮ
ዝም ነው ፀጥ ነው እሮሮን ዘንድሮ
* * *
ማርክስና ኤንግልስ ሌኒንም እያሉ
ማኦ፥ ቼ ጉቬራ፥ ሆ ቺ ሚኒ እያሉ
መሬትን ላራሹ ይሰጠው እያሉ
የዘንድሮ ልጆጭ ብዙ ጉድ አፈሉ
* * *
በእቅፍሽ ልውል ስል ክንድሽ እያፈነኝ
በካባሽ ላጌጥ ስል ክሳዱ እያነቀኝ
መናገሩን ፈቅደሽ በቀቀን ሁን ያልሺኝ
ባባትህ ተውና በኔ ስም ማልልኝ
ብለሽ የገረፍሺኝ ብለሽ የዘለጥሺኝ
ምዬም አልጠቀምኩሽ እምቢም ብል ላተዪኝ
ምናለበት ነበር ያንቺ ልጅ ባልሆንኩኝ
* * *
ለኩርማን እንጀራ ለስሙኒ ጠጅ
ሄደ አሉ ሰፈራ ይህ የወሎ ልጅ
* * *
ደርግና ኢሰፓ የሰሩብን ስራ
በሬያችንን ሞስኮ እኛን ግን ሰፈራ
* * *
ጨረቃና ኮኮብ ዛሬም እንዲያው ናቸው
ደርግና ኢሰፓ ባይለዋውጧቸው
* * *
ወይ አልተጣላነ አልተደባደብነ
ሰተት ብለው መጥተው ቤት አፍርሱ አሉነ
ወንዱም አላረሰ ሴቱም አላረሰ
እንደ ጥንብ አሞራ ቤት እያፈረሰ
* * *
አንዲት ጊደር ሸጬ ኢገማ ከፍዬ አኢወማ ከፍዬ
አኢሴማ ከፍዬ
ለናት ሀገር ጥሪ ለድርቅ ከፍዬ
ግብር ታክስ ላምራቾች ለሁሉ ከፍዬ
አንዲት ብር ቀርታኝ ሽልጦ ልገዛ ዐይኔ እህል ሲራብ
መንጥቆ ወሰዳት ለወታደር ቀለብ
እንዲህ ያለ ጊዜ የዘመን ቆረንጮ
ወልዶ ለዘመቻ ሰርቶ ለመዋጮ
* * *
ደርሶ ማንጎራጎር ልማዱ ነው ደሃ
እየቀዘቀዘው የሚጠጣው ውሃ
* * *
እሞታለሁ ብሎ ሰው ምነው ማዘኑ
ቅጠል አይበጠስ ካልደረሰ ቀኑ
* * *
እበላለሁ ጮማ እጠጣለሁ ጠጅ
እኔን ያስለቀሰኝ የድሃው ራብ እንጅ
* * *
ታርሶም ተሸምቶም ይበላል እንጀራ
እንደምነሽ ጥቃት የሞት ባልንጀራ
* * *
ያላግባብ የሆነ ብዙ ጉድለት ቢያውቅም
ሰው እርጥብ ነውና መቼም ነዶ አያልቅም
* * *
አለቅሳለሁ ባይኔ ሳዝን በወዳጄ
እንደ ሰማይ ኮኮብ እየራቀኝ ከጄ
* * *
ብለነው ብለነው ካልሆነ ነገሩ
ብርና ወንድ ልጅ የትም ነው ሀገሩ
* * *
ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበርታ
ላገር ብልጽግና ለወገን መከታ
* * *
ወንዞች ይገደቡ ይዋሉ ለልማት
በከንቱ ፈሰዋል ለብዙ ሺ ዓመታት
* * *
ፈጣን ነው ባቡሩ ፈጣን ነው ባቡሩ
ቆራጥ ያልሆናችሁ እንዳትሳፈሩ
http://ethiopianwebsite.arealion.yooco.org